ማኅበራዊ ኃላፊነት

ብዝኃነትና አካታችነት

Group of women | diversity & inclusion

በግርድፍ አነጋገር ብዝኃነትና አካታችነት ሰዎችን በዕድሜ፣ በጾታ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በአካል ጉዳት፣ በጾታዊ ግንኙነት ዝንባሌ፣ በትምህርት እና በብሔራዊ ማንነት አንዳቸውን ከሌላቸው ልዩ የሚያደርጋቸውን ሁኔታ በማክበርና ተገቢውን ዋጋ በመስጠት ሰዎችን ብቁ ማድረግ ማለት ነው። ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ ለብዝኃነትና አካታችነት ያለንን ቁርጠኝነት የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ፕሮግራሞችንና የሥልጠና ኮርሶችን ለሠራተኞቻችንና ለአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት ስናቀርብ ኩራት ይሰማናል።

የሴቶች የአመራርነት ትምህርት ቤት (WSOL)

Fairtrade Africa WSOL ዓላማውን የለውጥ ወኪሎችን/የጾታ እኩልነት ተሟጋቾችን በማቋቋም አማካኝነት ‹የጾታ እኩልነትን፣ አካታችነትንና የሴቶችና ወጣቶች እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን አቅምን ማጎልበትን ተግባራዊ ማድረግ› ያደረገ ኢኒሺየቲቭ ነው። ይህ የሚሳካው ሰብአዊ መብቶችና የጾታ እኩልነትን ማስፈንን፣ የገንዘብ አጠቃቀም ትምህርትና የፈጠራ ባለቤትነትን፣ የገቢ ምንጭ አድማስን ማስፋትን፣ የሴቶችና የአመራርነት ክኅሎቶች ልማትን ጨምሮ ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮችን በሚዳስሱት በ10 ሞጁሎች ላይ የአሠልጣኞች ሥልጠና (ToTs) መስጠት፣ ማለማመድ፣ ምክር መስጠትና የአቻ ለአቻ ትምህርት አቀራረቦችን በመከተል ነው። ከርዕሰ ጉዳዮቹ መካከል አንዱ ሴቶችን የራሳቸው የገቢ ማግኛ ሥራዎቻቸውን እንዴት ማስተዳደርና ማስፋት እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል። የWSOL ተሳታፊዎች የገቢ ማግኛ ሥራ የሚጀምሩበት የዘር መግዣ ገንዘብ/ካፒታል የሚሰጣቸው ሲሆን ይህም በዋናነት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ተሳታፊዎችና አካል ጉዳተኛ ሴቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል።
እ.ኤ.አ ከ2019 (2011 ዓ.ም.) ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ለሴቶች በምክር፣ ክኅሎት ማሳደጊያና የባሕሪ ለውጥ ኢኒሺየቲቮች አማካኝነት በሥራቸው ላይና በማኅበረሰባቸው ውስጥ መሪዎች እንዲሆኑ ድጋፍ ያደረጉላቸው የሥልጠና ሞጁሎችን ያጠናቀቁ የአበባ እርሻ ሠራተኞችን በሦስት ዙሮች አስመርቀናል።

እንደ ትምህርት ቤት ፕሮግራም አንድ ክፍል ለሴቶች የሥራ ዕቅዶቻቸውን እንዲያዘጋጁና የገቢ ምንጭ አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ድጋፍ ያደረጉላቸው ስምንት የገቢ ማግኛ የሥራ ምድቦች ተዘጋጅተዋል። የሼር ኢትዮጵያ የቀድሞ ምርት ሰብሳቢና የ2019 (2011 ዓ.ም.) ተመራቂ የሆነችው አዲስ ጴጥሮስ “የአመራርነት ትምህርቱ ለመማር ፍላጎት ብቻ በቂ እንደሆነ አስተምሮኛል። ፍላጎት ካለህ የአኗኗርህን የትኛውንም ክፍል ለችግር ሳታጋልጥ መማርና ማደግ ትችላለህ ” በማለት ትናገራለች።

ክብር ለሁሉም/Dignity For All (D4A)

በሼር ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን ማካተት ሁልጊዜም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ይህም ሆኖ ግን የFairtrade Africa ክብር ለሁሉም/Dignity for All ፕሮግራም (D4A) ለ116 አካል ጉዳተኛ ሠራተኞች ሥራቸውን የበለጠ ምቾት አግኝተው እንዲሠሩ የመሣሪያ ድጋፍ ያደርግላቸዋል። በዚህ ፕሮጀክት ሥር ሼር ኢትዮጵያና Fairtrade Africa የሚያስፈልገውን የመሣሪያ ዓይነትና በአግባቡ የሚገጥሙ መሣሪያዎችን ለመወሰን በሚያስችል መልኩ ለተጠቃሚዎች ልኬቶችን የመውሰድ ሥራ ለማከናወን ዝዋይ ከሚገኘው ግራርቤት መልሶ ማቋቋሚያ ማኅበር ጋር የቡድን ጥምረት ፈጥረዋል። መሣሪያዎቹ ባለ ሦስት እግር ብስክሌቶችን፣ ምርኩዞችን፣ ሰው ሠራሽ እግሮችን፣ የዓይን መነጽሮችንና የጆሮ መርጃ መሣሪያዎችን ያጠቃልላሉ። አምስት ሠራተኞች የግል ታሪኮቻቸውን ለማካፈል ፍቃደኛ ስለሆኑ በጣም እናመሰግናለን።

ስሜ ውብነሽ ታከለ ነው። ዕድሜዬ 22 ዓመት ሲሆን የመጣሁት ከወላይታ ሶዶ አካባቢ ነው። ለሼር ኢትዮጵያ ተቀጥሬ መሥራት የጀመርኩት ከ2018 (2010 ዓ.ም.) ጀምሮ ሲሆን ሥራዬ ለአበባ እንቡጦች መከላከያነት የሚያገለግሉ የአበባ እምቡጦችን ለክቶ ማስተካከል ነው። ይህ ተቀምጬ መሥራት የምችለው ዓይነት ሥራ ነው። የእግር ችግር ያጋጠመኝ ከ6 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ ሲሆን ከዚያ ጊዜ አንሥቶ በእግሬ ለመራመድ አስቸጋሪ ሆኖብኛል። ሆኖም በFairtrade የተሰጠኝ ሰው ሠራሽ እግር በእግሬ መራመድን ያቀለልኝ ከመሆኑም በተጨማሪ ሕይወቴን ወደተሻለ ሁኔታ ቀይሮልኛል።

Mohammed Kedir

ስሜ መሀመድ ከድር ነው። ዕድሜዬ 42 ዓመት ሲሆን ለሼር ኢትዮጵያ መሥራት የጀመርኩት ከ2009 (2001 ዓ.ም.) ጀምሮ ነው። በውትድርና አገልግሎት ሥር አገለግል በነበርኩበት ወቅት በጥይት ተመትቼ አንደኛው ዓይኔ በመጥፋቱ ምክንያት አርቴፊሻል ዓይን ተደርጎልኛል። ሌላኛው ዓይኔም ቀስ በቀስ የማየት አቅሙ እየተዳከመ መጥቶ ነበር። ለFairtrade ምሥጋና ይግባውና አሁን ሁለት ዓይነት የዓይን መነጽሮችን አግኝቻለሁ። አንደኛውን ለማንበብ የምጠቀምበት ሲሆን ሌላኛውን ደግሞ ለፀሐይ መከላከያ እጠቀምበታለሁ። ይህ የጥበቃ ሠራተኝነት ሥራዬን የበለጠ በራስ መተማመን እንድሠራ አስችሎኛል።

Selamawit Haile

ስሜ ሰላማዊት ሐይሌ ሲሆን ዕድሜዬ 22 ዓመት ነው። ለሼር ኢትዮጵያ መሥራት የጀመርኩት ከ2018 (2010 ዓ.ም.) ጀምሮ ሲሆን ከእህቴ ጋር አብሬ ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራት የመጣሁት ሾኔ (ሻሸመኔ) አካባቢ ነው። እኔና እህቴ የምንኖረው አብረን ሲሆን ሥራዬ የአበባ እቅፎችን ማዘጋጀት/bunch roses ነው። በልጅነቴ አንደኛው እግሬ ተሰብሮ የነበር በመሆኑ የተነሣ ከሌላኛው እግሬ ያጥራል። በFairtrade በተሰጡኝ ለእኔ ተስማሚ ተደርገው የተሠሩ ጫማዎች አማካኝነት የበለጠ እግሮቼን አመጣጥኜ መራመድ ችያለሁ። ይህ ትልቅ መሻሻል ከመሆኑም ባለፈ ለእግሮቼ ጥሩ ዕይታ ፈጥሮላቸዋል።

Mude Balcha

ስሜ ሙዴ ባልቻ ሲሆን ዕድሜዬ 47 ዓመት ነው። ትውልዴ ዐርባ ምንጭ ሲሆን በ2016 (2008 ዓ.ም.) ሥራ ለመፈለግ ስል ወደ ዝዋይ መጣሁ። በዚህም በሼር ኢትዮጵያ በመዝጋቢነት ተቀጠርኩ። በሕፃንነቴ በልጅነት ልምሻ በሽታ ተይዤ የነበረ በመሆኑ ምክንያት ይህም የቀኝ እግሬን ከግራ እግሬ እንዲያጥር አድርጎብኛል። በተሰጡኝ ለእኔ ተስማሚ ተደርገው የተሠሩ ሶሎችና ጫማዎች የተነሣ ግን እግር ኳስም ጭምር መጫወት እችላለሁ። ባለቤትም የፅጌሬዳ አበባ ማሳ/ እርሻ ሠራተኛ ነች። በጋራ ሆነን እየሠራን ዐርባ ምንጭ ከአጎታቸው ጋር እየኖሩ የሚገኙትን ልጆቻችንን ወደ ዩኒቨርሲቲና መላክና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ችለናል።

Addis Tadesse

ስሜ አዲስ ታደሰ ሲሆን ዕድሜዬ 21 ዓመት ነው። ወደ ሼር ኢትዮጵያ የተቀላቀልኩት በ2019 (2011 ዓ.ም.) ሲሆን እንደ የመጀመሪያ ሕክምና ርዳታ የሥራ ባልደረቦቼን መርዳት ያስደስተኛል። በመጀመሪያ የመጣሁት ከአርሲ በቆጂ ነው። የ2 ዓመት ሕፃን ሳለሁ እግሬን እሾህ ወግቶኝ ኢንፌክሽን ፈጥሮብኝ የነበረ በመሆኑ ምክንያት ይህ አንደኛው እግሬ ከሌላኛው እግሬ እንዲያጥር አድርጓል። ሆኖም Fairtrade የሰጠኝ ልዩ ሶሎችና ጫማዎች በእግሬ መራመድን በጣም አቅልለውልኛል። በቅርቡ በአካውንቲንግ በዲፕሎማ የተመረቅኩ ሲሆን ዲግሪዬን መማር እቀጥላለሁ። አንድ ቀን የቢሮ ሥራ እንደምይዝ ተስፋ አደርጋለሁ።

ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች/ ድርጅቶች ሥራ መፍጠር

ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች/ድርጅቶች (MSE) እንደ በጥሩ ሁኔታ ለገበያ መድረስ ባለ ተቋማዊ ድጋፍ ሲታገዙ ለሥራ አጦች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠርና ድህነትን ለመቀነስ የሚያስችል ጥሩ ስትራቴጂ ያቀርባሉ። እንደ ሼር ኢትዮጵያ አቅርቦቶችን ከ19 የተለያዩ የአካባቢ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የምንገዛ በመሆኑ ከ250 ለሚበልጡ ሰዎች የገበያ ትስሥር ፈጥረናል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በአዳሚ ቱሉ የሚገኘው በ8 ሰዎች (3 ወንዶችና 5 ሴቶች) የሚንቀሳቀሰው፣ና በአቶ ጆኒ ቡኔና ከድር አራርሶ የሚወከለው ዋይ.ኬ የንግድ ሥራ ነው። ቡድኑ በ2019 (2011 ዓ.ም.) ከተቋቋመ በኋላ ሥራውን የጀመረው ለሼር ኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን/ ግንባታ/ መምሪያ አሸዋ፣ ጠጠር፣ የተፈጨ ድንጋይና ቀይ አሸዋ በማቅረብ ነበር። ዋይ.ኬ በወር 17 ገልባጭ መኪናዎች የግንባታ ቁሳቁሶችን ያቀርባል። ከድር፦ ‘ባለፉት ዓመታት ውስጥ ቀስ በቀስ እንዴት የንግድ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ተምረናል። የመደራደር ክኅሎቶቻችን እየተሻሻሉ በመምጣታቸው ምክንያት በአሁኑ ወቅት የንግድ ሥራ አድማሳችንን ለማስፋት ለግንባታ ለሚውሉ ቁሳቁሶች አቅርቦት በመንግሥት በሚወጡ ጨረታዎች ላይም ጭምር ለመሳተፍ እንሞክራለን። ከስምንታችን የቡድኑ አባላት በስተጅርባ 22 ተጨማሪ የቤተሰብ አባላት አሉ። ስለሆነም በጠቅላላው ሼር ኢትዮጵያ በፈጠረልን የንግድ ሥራ ምክንያት 30 ሰው ተጠቃሚ መሆን ችሏል ማለት ነው። ከሥራችን በምናገኘው ገንዘብ የየራሳችንን የንንግድ ሥራዎችን ማቋቋም ለመጀመር ሐሳብ አለን’ በማለት ይናገራል።

የጾታ /ሥርዓተ ጾታ/ ፕሮግራሞች

የጾታ እኩልነቶችን ለማረጋገጥና የሴቶችን መብቶች ለማስከበር የተለያዩ ፖሊሲዎችን አዘጋጅተን ተግባራዊ አድርገናል። እነዚህ ፖሊሲዎች ከብዙ በጥቂቱ ስለ ወሲባዊ ትንኮሳ፣ አለማግለል፣ እኩልነትና ብዝኃነት፣ እንዲሁም የእናትነት እረፍትና ጡት ማጥባት በተመለከተ ያካተቱ ናቸው። እንደ ምሳሌ፦ የልጅ ተንከባካቢ/አሳዳጊ እናት ፖሊሲ እዚህ ላይ ተገልጿል፦
‘ስሜ አባይነሽ ሁሴን ሲሆን ዕድሜዬ 25 ዓመት ነው። በአዳሚ ቱሉ ለሼር ኢትዮጵያ መሥራት የጀመርኩት ከ3 ዓመት በፊት ነበር። በሥራዬ በግሪንሀውስ ውስጥ ምርት ሰብሳቢ ስሆን ባለቤቴ በሼር ኢትዮጵያ የመስኖ ልማት መምሪያ ውስጥ ሠራተኛ ነው። በትዳራችን ውስጥ አንድ የ3 ዓመትና አንድ 1 ዓመት ሊሞላው የደረሰ ሁለት ልጆችን አፍርተናል። ሼር ኢትዮጵያ የ4 ወራት ከክፍያ ጋር የሚሰጥ እረፍት ይሰጣል። በዚህ ላይ የዓመት እረፍቴ ሲጨመር ልጆቼን በወለድኩበት ወቅት ለ5 ወራት በቤት ውስጥ ማረፍ ችዬ ነበር። ልጄ ዕድሜው 1 ዓመት እስከሚሞላው ድረስ በቀን የሁለት ሰዓት ከክፍያ ጋር የሚሰጥ የጡት ማጥቢያ እረፍት የማግኘት መብት አለኝ። ስለሆነም በየቀኑ ልጄን ለማጥባት ከቀኑ 05፦00 ወደ ቤቴ ሄጄ ከቀኑ 07፦00 ሰዓት ላይ ተመልሼ ወደ ሥራ ቦታ እመጣለሁ። ከዚያም የሥራ ቀኔ ከቀኑ 09፦00 ሰዓት ማለትም ከሁሉም ሰው የሥራ ሰዓት ማብቂያ በአንድ ሰዓት ቀደም ብሎ የሚያበቃ በመሆኑ ወደ ልጆቼ ወደ ቤት መሄድ እችላለሁ። በቀኑ የሥራ ሰዓቴ ውስጥ እናቴ ልጆቼን የምትንከባከብልኝ በመሆኑ ለቤተሰቤ ገቢ ማምጣት እችላለሁ። ትልቋ ልጄ ዕድሜዋ 4 ዓመት ሲሞላት ያለ ምንም ክፍያ በሼር ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ለትምህርት አስመዘግባታለሁ። ይሄኛው ደግሞ ለሼር ኢትዮጵያ መሥራት የሚያስገኘው ሌላኛው ጥቅም ነው’።

የአቻ አስተማሪዎች

ሠራተኞቻችንን ስለተለያዩ የብዝኃነትና አካታችነት ርዕሰ ጉዳዮች ለማስተማር የአቻ አስተማሪዎችን እንጠቀማለን። የአቻ ትምህርት ሌሎች ተመሳሳይ ማኅበራዊ መነሻዎችን ወይም የሕይወት ተሞክሮዎችን ሊጋሩ የሚችሉ ሰዎችን ከማስተማር ጋር በተያያዘ ስለ ጤና መረጃ፣ ዕሴቶችና ባሕሪ ማስተማር ወይም ማጋራት ነው። የአቻ አስተማሪዎች ዓመቱን በሙሉ የተለያዩ የሥልጠና ክፍለ ጊዜዎችን ይወስዱና ሠራተኞቻችንን በፍቃደኝነት ያስተምራሉ። ከእስተማሪዎቹ መካከል ሁለቱን ስለ ተሞክሮዎቻቸው እንዲነግሩን ጠይቀናቸዋል። ከሁለቱ አንደኛዋ ቦዶዴ ቂልጦ ነች። ኩሩ የ26 ዓመት ሴት ወይዘሮ ስትሆን መሳጭ ታሪኳ የሚከተለው ነው፦
‘ተወልጄ ያደግኩት አዳሚ ቱሉ ውስጥ ሲሆን ለሼር ኢትዮጵያ መሥራት የጀመርኩት ከ9 ዓመታት በፊት ገደማ በካርቶን አደራጅነት ተቀጥሬ ነው። ከመጀመሪያው ዓመት አገልግሎቴ በኋላ ለአካል ጉዳቴ የሕክምና እንክብካቤ ማግኘት ችዬ ነበር። የ15 ዓመት ልጅ እያለሁ የልጅነት ልምሻ በሽታ ይዞኝ የነበረ በመሆኑ ምክንያት ይህም እግሬን በጣም ቀጭን እንዲሆን አድርጎታል። ከዚህ ጊዜ አንሥቶ የምራመደው ምርኩዞችን በመጠቀም ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ አገኘሁ። በ2017 (2009 ዓ.ም.) በድርጅቱ የጥራት መምሪያ ውስጥ ሥራ ተሰጠኝ። የጥራት ተቆጣጣሪነት ኃላፊነት የተሰጠኝ ከመሆኑም በተጨማሪ የሥርዓተ ጤና ኮሚቴና የጤናና ደኅንነት ኮሚቴ አባል ነኝ። አካል ጉዳተኛ ብሆንም ሼር ኢትዮጵያ ብዙ ትላልቅ ዕድሎችን ሰጥቶኛል። የሥራ ባልደረቦቼን በሁሉም ዓይነት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማስተማር በተለይም ለአካል ጉዳተኞች ግንዛቤ መፍጠር ደስ ይለኛል። በቅርቡ በFairtrade ክብር ለሁሉም/Dignity for all ፕሮግራም ሰው ሠራሽ እግር ተሰጥቶኛል። አሁን በጣም ከረጅም ጊዜ በኋላ ያለ ምርኩዞች ድጋፍ መራመድ ችያለሁ። እጅግ ደስተኛና ኩራት የሚሰማኝ ሰው ነኝ። በቅርቡ ትዳር የመሠረትኩ ሲሆን እውነተኛ የመባረክ ስሜት ይሰማኛል።’

ሌላኛዋ የአቻ አስተማሪ የ28 ዓመት ዕድሜ ያላት እየሩሳሌም በየነ ነች፦
‘ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የጀመርኩት ከ2013 (2005 ዓ.ም.) ጀምሮ ሲሆን በተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ ማለትም፦ 2 ዓመት በጠቅላላ ሠራተኝነት፣ 2 ዓመት በመዝጋቢነትና ባለፉት 4 ዓመታት ውስጥ በመጋዘን ኃላፊነት ሠርቻለሁ። የመጣሁት ከወንጂ አካባቢ ሲሆን የ8 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድ ልጅ አለኝ። እንደ የአቻ አስተማሪነታችን እንደ የጾታ እኩልነት፣ የሴቶችን አቅም ማጎልበትና የቤተሰብ ዕቅድ በመሳሰሉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቋሚ የውስጥና ውጫዊ ሥልጠናዎችን እንወስዳለን። በሳምንት አንድ ጊዜ የሥራ ባልደረቦቻችንን ከ25 እስከ 50 ሰው በሚይዙ ቡድኖች በመክፈል ሥልጠና እንሰጣቸዋለን። ምሳ ሰዓት ላይ የተማርነውን ትምህርት ለማስተላለፍ እንሞክራለን። ሰዎች ሲቀየሩና በሕይወታቸው ውስጥ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ ማየት ያስደስተኛል። እነዚህ ሁሉም ዕውቀቶች የበለጠ በራስ መተማመንና ለራስ ክብር ያለኝ ሴት እንድሆን አስችሎኛል። ለምሳሌ በFairtrade ፕሪሚየም ኮሚቴ የሚቀርበውን ሥልጠና መጥቀስ ይቻላል። ባለፈው ዓመት የ6 ወራት ሥልጠና የተከታተልኩ ሲሆን በቅርቡ በኮሌጅ ለ3 ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ፕሮግራም ተመዝግቤያለሁ’።

ሌላኛዋ የአቻ አስተማሪ የ28 ዓመት ዕድሜ ያላት እየሩሳሌም በየነ ነች፦

ሌላኛው እጅግ አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳይ የቤተሰብ ዕቅድና ኤችአይቪ ኤድስን መከላከል። የአቻ አስተማሪ የሆነችው ቤዛ ኢፕሳ (33 ዓመት) ሌሎችን ለማስተማር የራሳቸውን ታሪክ ከሚጠቀሙ ሠራተኞቻችን መካከል አንዷ ነች፦
‘በመጀመሪያ የመጣሁት ከአርሲ ሲሆን ዝዋይ ውስጥ ወደ 20 ዓመታት ያክል ኖሬያለሁ። ለሼር ኢትዮጵያ መሥራት የጀመርኩት በ2014 (2006 ዓ.ም.) ነው። የመጀመሪያዎቹን 6 ወራት በጥበቃ ሠራተኝነት የሠራሁ ሲሆን ቀጥሎ ያሉትን 2 ዓመታት የአነስተኛ መጋዘን ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ሠርቻለሁ። ከ2017 (2009 ዓ.ም.) ጀምሮ ከዋና ዋና መጋዘኖች መካከል የአንዱ ኃላፊ ሆኜ እየሠራሁ ነው። ከ5 ዓመታት በፊት የሥርዓተ ጾታ ኮሚቴን የተቀላቀልኩ ሲሆን የሥራ ባልደረቦቼን የግል መከላከያ መሣሪያን (PPE) ስለመጠቀም፣ ንጽሕናን ስለመጠበቅና ስለ ቤተሰብ ዕቅድ አስፈላጊነት አስተምራለሁ። ከራሴ ተሞክሮ በመነሣት በልጅነት ዕድሜ ማግባት ሸክም እንደሆነ አውቃለሁ። ያገባሁት በ13 ዓመቴ ሲሆን የመጀመሪያ ልጄን የወለድኩት በ14 ዓመት ዕድሜዬ ነበር። የመጀመሪያ ልጄ አሁን ዩኒቨርሲቲ የገባ ሲሆን ሁለተኛው ልጄ በሼር ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ውስጥ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። ሦስተኛውን ልጄን ፍቅር ብዬ የምጠራው ሲሆን አሁን የ2ኛ ክፍል ተማሪ ነው። እንደ መታደል ሆኖ ያገባሁት ጥሩ ሰው ነው። የመጀመሪያ ሁለቱን ልጆቼን ከወለድኩ በኋላ ተመልሼ ትምህርት መማር ጀምሬ የነበረ ሲሆን 8ኛ ክፍል ካጠናቀቅኩ በኋላ በአካውንቲንግ ዲፕሎማዬን ለማግኘት የሦስት ዓመታት የቀን ትምህርት መከታተል ነበረብኝ። ትምህርት እየተከታተሉ ልጆች ማሳደግ ለእኔ ከባድ ጊዜ ነበር። ሆኖም ገፍቼ በመቀጠሌ ደስተኛ ነኝ። ህልሜ በድጋሚ ትምህርቴን መከታተል ነው። ሁለተኛው ልጄ ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደገባ ወዲያውኑ የአካውንቲን ትምህርቴን ቀጥዬበት ዲግሪ ማግኘት እፈልጋለሁ። ለሁሉም ወጣት ልጃገረዶች የምነግራቸው ቤተሰብ ከመመሥረታቸው በፊት ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ነው። እንዲሁም እራሳቸውን ከወሲባዊ ትንኮሳና ኤችአይቪ ኤድስ መከላከል እንዳለባቸው እመክራቸዋለሁ። በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ማግኘት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ታሪኬን የምናገረው ኩራት እየተሰማኝ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሌሎች ግንዛቤ ፈጠራ አስተዋጽኦ ማድረግ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ።’

የሥነ ተዋልዶ ጤና

ሠራተኞቻችንን ስለ ሥነ ተዋልዶ ጤና ማስተማር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለች የሕዝቧ አማካኝ ዕድሜ 19.8 ዓመትና ጠቅላላ የሕዝብ ብዛቷ ወደ 115 ሚሊዮን የሚጠጋ ለሆነባት አገር የወሊድ ቁጥጥር ወሳኝ ነው። ነርስ ጫልቱ ዎራና (38) ስለዚህ አስፈላጊነት በመገንዘብ እንዲህ ትላለች፦ ‘ለሼር ኢትዮጵያ መሥራት የጀመርኩት ከ2014 (2006 ዓ.ም.) ጀምሮ ነው። በአዋላጅነት ዲፕሎማ ያገኘሁ ሲሆን ለ7 ዓመታት በሼር ኢትዮጵያ ሆስፒታል ውስጥ ሠርቻለሁ። በ2020 (2012 ዓ.ም.) በእርሻ/ማሳ ላይ የኩባንያው ነርስ ተደርጌ ተመድቤያለሁ። በየዕለቱ ጠዋት ላይ ወደ ግሪን ሀውሶችና ደረጃ መዳቢዎች የምሄድ ሲሆን እዚያም እንደታመሙ ሪፖርት ያደረጉ ሠራተኞችን እመረምራለሁ። ከሰዓት በኋላ ቢሮዬ ለግል ምክር አገልግሎት ክፍት ሲሆን ለብዙ ሠራተኞች ስለ ቤተሰብ ዕቅድ፣ የወሊድ ቁጥጥር፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት ስለሚተላለፉ በሽታዎችና አላስፈላጊ እርግዝና የምክር አገልግሎት እሰጣቸዋለሁ። በብዙኃን ትምህርትና የግንዛቤ ፈጠራ ሥልጠና አማካኝነት ለሠራተኞቻችን ዕውቀት ለማስጨበጥ እንሞክራለን። በአቻ አስተማሪ ፕሮግራም ሥር አሠልጣኞችን የማሠልጠን ሲሆን በጣም ብዙ የሥራ ባልደረቦችን ማዳረስ ችለናል። ባለፈው ዓመት ወጣት ልጃገረዶችን የወሊድ መቆጣጠሪያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ በማሳመን ረገድ እጅግ ስኬታማ ሆነናል። በተጨማሪም በሼር ኢትዮጵያ ሆስፒታል ውስጥ ለኤችአይቪ ኤድስ ታማሚዎች የምክር አገልግሎት የምንሰጥ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሁሉም ዕድሜያቸው ከ30-50 ዓመት ለሆኑ8 ሴቶች የማህጸን ካንሰር ምርመራዎችን እናደርጋለን።’