ማኅበራዊ ኃላፊነት

ርትዓዊ የንግድ ውድድር

Fairtrade
ርትዓዊ የንግድ ውድድር ምንድን ነው?

Fairtrade ሰዎችን በተሻሉ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሠሩና ኩባንያዎችን/ሠራተኞችን ለሚያመርቱት ምርት ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያገኙ የሚረዳ ማኅበራዊ ንቅናቄ ነው። ይህ ለሠራተኞች አኗኗራቸውን የሚያሻሽሉበትና ለወደፊት የሚያቅዱበት ዕድል ይሰጣቸዋል። Fairtrade የታዳጊ አገራት ዜጎችን ምርቶቻቸውን ለአደጉት አገራት ዜጎች ለመሸጥ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የሚሸጡ ምርቶች የዕደ ጥበብ ውጤቶችና ሌሎች የተፈበረኩ ዕቃዎችን እንዲሁም እንደ ጥራጥሬዎች፣ ቡና፣ ካካዎ፣ ስኳር፣ ሻይ ቅጠል፣ ሙዝ፣ ማር፣ ጥጥ፣ ኩዪኖዋ፣ ትኩስ ፍራፍሬዎች፣ ቼኮሌትና አበባዎች የመሳሰሉ የግብርና ምርቶችን ያጠቃልላሉ። የርትዓዊ ንግድ ደረጃ ያገኘ ሸቀጥ የFairtrade ማረጋገጫ/የምስክር ወረቀት የሚሰጠው ሲሆን ይህም ለሠራተኞችና አካባቢ ፍትሐዊነትን የተመለከቱ ሕጎችን እንደሚያሟላ ያመለክታል። ሼር ኢትዮጵያ በ2012 (2004 ዓ.ም.) የFairtradeን የምስክር ወረቀት ያገኘ ሲሆን ከዚህ ጀምሮ ሕጎቹን ያከብራል። የፅጌረዳ አበባዎቻችንን ለFairtrade በመሸጥ የምናገኘው ፕሪሚየም/አረቦን በማኅበረሰቦች ውስጥ ኢንቨስት እንድናደርግ ያስችለናል። በ ትምህርት እና ጤና ከምናካሂዳቸው ጠቃሚ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የFairtrade ፕሪሚየም/አረቦን ኮሚቴ እራሱን ችሎ የተለያዩ ከዚህ በታች የተገለጹትን ፕሮጀክቶች ያካሂዳል። ከዚህ በተጨማሪም በFairtrade Africa ፕሮግራሞች ላይ በትብብር እንሠራለን፤ ለምሳሌ DignityforAll and the Women School of Leadership

የFairtrade ፕሪሚየም ኮሚቴ ክፍል

አምስት የFPC አባላት

ከግራ ወደ ቀኝ፦ ከሊል ገዳ (ሰብሳቢ)፣ ከድር አበበ (ግምጃ ቤት)፣ በላይነህ ጌታቸው (ምክትል ሰብሳቢ)፣ አብዱቃድር ሴማ (የሂሳብ ባለሙያ)ና አንዷለም አበራ (የጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ)

የFairtrade አረቦን/ፕሪሚየም ኮሚቴ (FPC) ተመራጭ የሠራተኛ አባላትንና የአስተዳደር ተሿሚ አማካሪዎችን የሚይዝ ኮሚቴ ነው። የኮሚቴው ዓላማ ለሁሉም ማረጋገጫ ያገኘ እርሻ/ማሳ ሠራተኞች ጥቅም እንዲውል የሚሰጠውን የFairtrade አረቦን ማስተዳደር ነው።

የሼር ኢትዮጵያ የFPC ፕሮጀክት 1፦ ድጎማ የሚደረግለት የምግብ አቅርቦት

ርትዓዊ የንግድ ውድድር ፕሪሚየም ኮሚቴ ለሼር ኢትዮጵያ ሠራተኞች በ30% የተመን ድጎማ ምግብ ያቀርባል። የሚቀርቡት የምግብ ምርቶች የምግብ ዘይትን፣ በቆሎንና የስንዴ ዱቄትን የሚያጠቃልሉ ሲሆን ለሠራተኞች በየወሩ ይቀርባሉ። ድጎማ የሚደረግለት ምግብ በኢትዮጵያ ባሉት ያልተረጋጉ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች የተነሣ በመላው አገሪቱ የምግብ ዋጋዎች በመጨመራቸው ምክንያት የተፈጠረውን የዋጋ ግሽበት እንዲቋቋሙ ይረዳቸዋል።

የሼር ኢትዮጵያ የFPC ፕሮጀክት 2፦ በክኅሎት ሥልጠናዎች አማካኝነት የሚካሄድ የአቅም ግንባታ

አቅም ግንባታ ከርትዓዊ የንግድ ውድድርዓላማዎች መካከል አንዱ ነው። ስለሆነም የፕሪሚየም/አረቦን ኮሚቴው በየዓመቱ የክኅሎት ሥልጠናዎችን ለማዘጋጀት የሚውል በጀት ይመድባል። በ2021 (2013 ዓ.ም.) ለሁሉም የሼር ኢትዮጵያ ሠራተኞች ክፍት የሆኑ 4 የተለያዩ ዓይነት የክኅሎት ሥልጠናዎች የሚሰጡ ሲሆን እነዚህም በውበት ሳሎን፣ ልብስ ስፌት፣ የመንጃ ፍቃድና ኮምፒውተር ላይ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ናቸው። እስከ አሁን ድረስ ከ800 በላይ ሠራተኞች ለሥልጠናዎቹ የተመዘገቡ ሲሆን 60% የሥልጠና ወጪዎቹ በኮሚቴው በሚመደበው ገንዘብ ይሸፈናሉ። ለ40% ወጪዎቹ ደግሞ ሠራተኞች አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይህ የሚደረገው ሁሉንም ተሳታፊዎች ተነሣሽነት እንዲኖራቸው ለማድረግ ነው። ሥልጠናዎቹ የሚሰጡት በግል ኮሌጆች ሲሆን ሠራተኞች ሥልጠናዎቹን ከሥራ ሰዓቶች በኋላ ሊከታተሉ ይችላሉ። ይህ ፕሮጀክት ለሠራተኞቻችን ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትና እራሳቸውን የሚያበቁበት ዕድል በመስጠት ሠራተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል። ኮርሶቹ በአማካኝ 8 ወራት የሚወስዱ ሲሆን እንደ ሥልጠናው ዓይነት ላይ ተመሥርቶ ተሳታፊዎችን በሳምንት ከ3 እስ6 ሰዓቶች ያክል መገኘት ይጠይቋቸዋል። ከ(ቀድሞ) ተሳታፊዎች መካከል ጥቂቶቹን ስለ ታሪኮቻቸው እንዲያካፍሉን ጠይቀናቸዋል። ታሪኮቹን ከታች ማንበብ ትችላላችሁ።

ፕሮጀክት 2፦ የክኅሎት ሥልጠናዎች እማኞች

የውበት ሳሎን

መለሰ በቀለ

ስሜ መለሰ በቀለ ሲሆን ዕድሜዬ 30 ዓመት ነው። ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የጀመርኩት በ2007 (1999 ዓ.ም.) በደረጃ ምደባ ውስጥ በአበባ ጠቅላይነት ተቀጥሬ ነበር። በ2009 (2001 ዓ.ም.) የጽዳት ኃላፊ ተደርጌ የተሾምኩ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በዚሁ ኃላፊነት ላይ እየሠራሁ እገኛለሁ። ትዳር መሥርቼ የ5 ዓመት ሴት ልጅ የወለድኩ ሲሆን በጸጉር ማስተካከል ሙያ የወሰድኩት ሥልጠና ወደፊት ገቢዬን እንዳሳድግ ይረዳኛል። የሼር ኢትዮጵያ ሥራዬን እየሠራሁ በቤቴ ውስጥ ጸጉር ቤት መክፈት እፈልጋለሁ። የጸጉር መቁረጥ ሥራ በትርፍ ጊዜዬ ልሠራው የምችለው ዓይነት ደሥራ ነው።

ልብስ ስፌት

ማስረሻ ተሰማ

ስሜ ማስረሻ ተሰማ ሲሆን ዕድሜዬ 20 ዓመት ነው። ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የጀመርኩት በ2018 (2010 ዓ.ም.) በጽዳት መምሪያ ውስጥ ተቀጥሬ ሲሆን አሁን የቢሮ ረዳት ሆኛለሁ። ተወልጄ ያደግኩት ዝዋይ ውስጥ ሲሆን አሁንም የምኖረው ከእናቴና ከ18 ዓመት ወንድሜ ጋር ነው። ወንድሜ በ2022 (2014 ዓ.ም.) በፋሽን ዲዛይነርነት የሚመረቅበት ሲሆን በዚህ ወቅት የራሳችንን ሱቅ መክፈት እንፈልጋለን። ይህ የክኅሎት ሥልጠና በብዙ መልኩ ረድቶኛል። በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቅቄ የዲፕሎማ ትምህርት ለመከታተል ያስችለኝ ዘንድ የ11ኛና 12ኛ ክፍል ትምህርቴን ለማጠናቀቅ የማታ እየተማርኩኝ ነው።

መንጃ ፍቃድ

ሳዳም ኮርማ

ስሜ ሳዳም ኮርማ ሲሆን ዕድሜዬ 26 ዓመት ነው። ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት የጀመርኩት በ2015 (2007 ዓ.ም.) በደረጃ ምደባ መምሪያ ውስጥ ተቀጥሬ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የመጋዘን ኃላፊ ሆኛለሁ። ተወልጄ ያደግኩት ዝዋይ ውስጥ ነው። በነሀሴ ወር 2021 (2013 ዓ.ም.) የአሽከርካሪነት ክኅሎት ሥልጠናዬን አጠናቅቄ አሁን ብቁ የአውቶቡስ ሹፌር ሆኛለሁ። ገቢዬን ማሳደግ ያስችለኝ ዘንድ በትርፍ ጊዜዬ በሹፌርነት ለመሥራት እያሰብኩኝ ነው።

ኮምፒውተር

ሚኪያስ ደጉ

ስሜ ሚኪያስ ደጉ ሲሆን ዕድሜዬ 24 ዓመት ነው። በሼር ኢትዮጵያ ግሪንሀውስ ጥገና ክፍል ውስጥ ተቀጥሬ መሥራት የጀመርኩት በ2019 (2011 ዓ.ም.) ነው። ሦስት ልጆች ያሉኝ እንደመሆኑ የሥራ መደቤን የመሳደግ ፍላጎት አለኝ። የአይቲ ዕውቀት ሳገኝ አንድ ቀን የቢሮ ሥራ ፈልጌ እንደማገኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ትምህርቱ ሲጀምር ብዙን ጊዜ የሚወስደው የንድፈ ሐሳብ ትምህርት ሲሆን አሁን እንደ ኤምኤስ ኦፊስ ያሉ የተግባር ፕሮግራሞችን ተምረናል።

የሼር ኢትዮጵያ የFPC ፕሮጀክት 3፦ በድህነት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች የሚሰጥ የማኅበረሰብ መኖሪያ ቤት

ኮሚቴው በቅርቡ ከአረቦን ፈንዱ ውስጥ ከፍተኛው የገንዘብ መጠን ዝዋይ ውስጥ የሚገኙ የአንዳንድ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ የማኅበረሰብ አባላትን የመኖሪያ ቤት ሁኔታ ለማሻሻል እንዲከፈል ወስኗል። ከከተማው አስተዳደር ጋር በመተባበር 16 ቤተሰቦች 16 አዲስ አፓርታማዎችን/ የጋራ መኖሪያዎችን የመገንባት ዓላማ ያለው የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተመርጠዋል። ይህ የማኅበረሰቡ አባላትን ቀደም ሲል ያጡትን ሰላማዊ መኖሪያ ቤትና ንጹሕ የመጸዳጃ አገልግሎቶች እንዲያገኙ በማስቻል ጤናማ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር ያስችላል። ይህ በሼር ኢትዮጵያ የFairtrade ፕሪሚየም/አረቦን ኮሚቴ ኃላፊነት ሥር የሚካሄድ የ1.6 ሚሊዮን ኢት ብር ፕሮጀክት ነው። ሼር ኢትዮጵያ ለፕሮጀክቱ የ320,000 ኢት ብር ልገሳ ለመስጠት የተስማማ ሲሆን ይህም በግንባታ ቡድኑ አማካኝነት በሰው ኃይል/ጉልበት መልኩ የሚደረግ አስተዋጽኦ ነው።