Category Archives: News

Overview News

ክፍት የሥራ ቦታ፦ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር

6 September 2022 Aswin Endeman

በአዳሚ ቱሉ ለሚገኘው የሼር ኢትዮጵያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አወዳድረን መቅጠር እንፈልጋለን።

በጣም ጥሩ የሆነ ከሰው ጋ የመግባባትና የማደራጀትና የመምራት ችሎታ አለኝ ብለው ያምናሉ? ቡድንን ማስተባበርና መምራት ይችላሉ? ቢቻል በግል ወይም በሕዝብ ትምህርት ቤት ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ቢያንስ የ 3 ዓመታት የሥራ ልምድ ያለውን ባለሙያ እንፈልጋለን። ከርስዎ የምንፈልገው ቁርጠኛ እንዲሆኑና ቀና አመለካከት ያልዎት እንዲሁም ተማሪዎቻችን ያላቸውን እምቅ ችሎታ እንዲያወጡት እንዲያግዟቸው ነው!

በያወጣነውን ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ከተመለከቱ በኋላ በእነርሱ የድርጣቢያ (ዌብሳይት) በኩል እባክዎ ማመልከቻዎን ያስገቡ።

Overview News

የደን ልማትና ክብካቤን ለማሳደግ የተደረገ የ57.000 ችግኝ ተከላ መርሃግብር

22 July 2022 Aswin Endeman

በዓመታዊው የኢትዮጵያ የ 2014 ዓ.ም. የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ፣ የችግኝ ተከላ ወቅት፣ ሐምሌ 11 ቀን በዝዋይ/ ባቱ ዎርጃ ተራራ ላይ እና በቆቃ በርካታ ችግኞች /በቁጥር 57.000 ተክለናል። በዚህም ምክንያት ከ 2009 ጀምሮ የተከልናቸውን ችግኞች ብዛት ወደ 1 ሚሊዮን እንዲጠጋ ለማድረግ ችለናል። ዘላቂነት ያለው የደን ጥበቃ ማድረግን እና የርጃ ተፋሰስን በብልሃት ተጠቃሚ መሆን መቻልን ማረጋገጥ ዋንኛ ዓላማው በሆነው በዚህ ፕሮጄክት ሥር፣ ሼር፣ አይዲኤች እና ቪክዳ የደን መራቆትን እና የአየር ንብረት መዛባትን በሚከተሉት ጥረቶች ለመዋጋት አንድ ላይ በትብብር በመሥራት ላይ ይገኛሉ፦

  • የደን ልማትና ክብካቤ እና ኤኮ-ቱሪዝምን ማልማት (በግምት 285 ሄክታር የወል መሬት)
  • የተጎዱ አካባቢዎች ላይ ትናንሽ ሸለቆዎችን በመቆፈርና የአፈር መሸርሸርን መከላከያ የግንብ አጥሮችን በመሥራት እንዲያገግሙ ማድረግ
  • የሚታጨድ ሣር ዘርን መዝራትና የከብት መኖ አጠቃቀምን ማሻሻል
  • ገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴ የሚያከናውኑ ቡድኖችን ማቀናጀት (ለአብነት ንብ ማነብ ሥራ)
  • ጥሩ የእርሻ ዘዴዎችን ማስተማርና ተፈጻሚ ማድረግ፣ ለምሳሌ የአካባቢው አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር እንዲጠቀሙ ማድረግ

የመጨረሻው ግብ ፕሮጄክቱ በማኅበረሰቡ በራሱ እንዲታዳደርና ጥበቃ የተደረገለትን አካባቢ በባለቤትነት እንዲይዝ ማድረግ ነው።

9 የተለያዩ አገር በቀል የዛፍ ዓይነቶችን እንድንተክል ላገዙን ለሠራተኞቻችን እና ለሁሉም በጎ ፈቃድ ተሳታፊዎች በሙሉ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

Overview News

የማሕፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ

22 July 2022 Aswin Endeman

ሼር ኢትዮጵያ ሆስፒታል ግራውንድስ ፎር ሄልዝ (Grounds for Health) ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ዕድሜያቸው ከ 30-50  ውስጥ ለሚገኙ ሴት ሠራተኞቻችን ነጻ የማሕፀን ጫፍ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል ዘመቻ አስጀምረናል። የዘመቻዉም ዓላማ ሴት ሠራተኞች በመሀፀን ካንሰር በሽታ እንዳያዙ ለመከላከልና በሽታውን በሕክምና መዳን በሚችልበት ደረጃ ላይ እያለ መኖሩ ከታወቀ በኃላ አስፈላጊውን ሕክምና መጀመር እንዲቻል ማድረግ ነው። ምርመራው የማሕፀን ሕዋሳትን ጤና እንዲዛባ የሚያደርገውን ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ / ኤችፒቪ/ (human papilloma virus /HPV ) የሚባለውን አደገኛ ቫይረስ መኖር እና አለመኖሩን ያጣራል። አብዛኛዎቹ የማሕፀን ካንሰር ዓይነቶች ከአደገኛው ኤችፒቪ ቫይረስ ጋ ግንኙነት አላቸው።

የግራውንድስ ፎር ሄልዝ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ደምስ እንደሚሉት በሠራተኞች መካከል ስለ በሽታው ግንዛቤ እንዲኖር ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። እሳቸው ከሕክምና ቡድናቸው ጋ አንድ ላይ በመሆን በነፍስ ወከፍ ምርመራ ከመደረጉ በፊት በአነስተኛ ቡድኖች ለተደራጁ ሠራተኞች የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ። ድንገት ሠራተኛዋ ውጤቷ ፖዘቲቭ ሆኖ ቢገኝ፣ ሕክምናው ይሰጣታል። የግራውንድስ ፎር ሄልዝ ሥር የሚሠሩትን እነዚህን አጋሮቻችንን ለሚያደርጉልን ድጋፍ በሙሉ እያመሰገንን ሁሉም ሴቶቻችን ተሳታፊ እንዲሆኑ ከወዲሁ እንጋብዛለን።

Overview News

የትምህርት ዓመቱ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት

20 July 2022 Aswin Endeman

በዚህ ሳምንት በኛ የሼር ትምህርት ቤቶች ውስጥ የ 2014 ዓ.ም. ትምህርት ዘመንን መዝጊያ ሥነ ሥርዓት አክብረናል። በዝዋይና በአዳሚ ቱሉ በሚገኙት ትምህርት ቤቶቻችን ውስጥ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ ወላጆችና ተጋባዥ እንግዶች በሥነ ሥርዓቶቹ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል። ዝግጅቶቹ በግጥም ንባብና በባህል ትርዒቶችና ጭፈራዎች የታጀቡ ደስ በሚያሰኙ ውብ ክንውኖች የታጀቡ ነበሩ። የመዋለ ሕፃናት ተመራቂ ተማሪዎች ጥቁር ጋውናቸውንና ጥቁር ባርኔጣቸውን አድርገው ለዝግጅቱ ድምቀት ሆነዋል። የሼር ሥራ አስኪያጆችና የትምህርት ቢሮ ተወካዮች በሥነ ሥርዓቶቹ ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል። የዓመቱ ምርጥ ተማሪዎችና መምህራን የምስክር ወረቀትና ሽልማቶች ተሰጥተዋቸዋል። ሁለት ስኬታማ ቀናትን በአጭሩ አሳልፈናል።

በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ሕፃናት ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት ያለ ምንም ክፍያ በመስጠት ሼር ኢትዮጵያ በርካቶችን ብሩህና የተሻለ መፃኢ ጊዜን ተስፋ እንዲያደርጉ አድርጓቸዋል። የድርጅቱን አንጋፋ መሪዎች አርአያነት በመከተል ሚስተር ጌሪት እና ሚስዝ ኔል ባርንሁርን ይህ የሕፃናቱ ተስፋ እንደለመለመ እንዲቆይ ለማድረግ ቁርጠኝነታቸው አሁንም እንደተጠበቀ ነው።

Overview News

ለ IGA የሚሰጥ ድጋፍ፦ ንብ ማንባትና ሥነ ምኅዳርን የጠበቀ ቱሪዝም አገልግሎት

10 July 2022 Aswin Endeman

አፍሪፍሎራና ሼር ሥራቸውን በሚያከናውኑባቸው አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ለማጠናከር እንዲቻል ከራሳቸው ከማኅበረሰቦቹ ለተውጣጡ ቡድኖች የተለያዩ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ እንቅስቃሴ የሚደረጉባቸውን በርካታ ፕሮጄክቶች ድጋፍ ይሰጣሉ። ባለፉት ወራት ብቻ በርካታ ቡድኖች በንብ ማንባትና ሥነ ምኅደርን የጠበቀ ቱሪዝም አገልግሎት ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል።

ከ 4 እስከ 10 አባላት ላሏቸው 13 ቡድኖች 50 የንብ ቀፎዎች ተከፋፍለዋል። በድምሩ 80 ሰዎች ስለ ማር ምርት አመራረት መሠረታዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል። ከእያንዳንዱ የነዚህ ፕሮጄክት አባል የሆነ ሰው ጀርባ ተጠቃሚ የሆኑ ብዙ ቤተሰቦች አሉ። እዚህ ላይ እንደ አብነት ለመጥቀስ ያህል፣ ሙስጠፋ አቡ ንዑስ ቡድን/አፒያሪ የተባለው (ፎቶ ላይ የሚታየው) ቡድን ነው። የዚህ ቡድን አባላት በማር ምርት ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን ማር ሸጠው ከሚያገኙት ገንዘብ አብዛኛውን ተጨማሪ የንብ ቀፎ ለመግዛት ሊጠቀምበት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። አንድ ላይ ተባብሮ በመሥራት አንድን ቤተሰብ ብቻ ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ መላው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ከምርቱ የተወሰነው ክፍል ራሳቸው አማራቾቹ የሚጠቀሙበትም ይሆናል።

ከወርጃ ዋሽጉላ እና ካሞ ገርቢ አካባቢ የመጡ ሥነ ምኅደርን በጠበቀው ፕሮጄክት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ 20 ተጠቃሚዎች (በሙሉ ወጣቶች ናቸው) በወርጂ ኮረብታ ወደ የሚገኘው የሥነ ማኅደር ማዕከል የሚመጡ ቱሪስቶችን ተቀብለው ለማስተናገድ የሚያስችላቸውን ሥልጠና ወስደዋል። ይህ አካባቢ ብዙ ዓይነት አእዋፍና እጅግ የሚያምር መልክዓ ምድር ያለው ቦታ ነው። በሥነ ሥርዓቱ መክፈቻ ላይ ከ 200 በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን በዝግጅቱም የባህል ምግቦችንና ተወዳጁን የኢትዮጵያ ቡና አጣጥመዋል። ምግቦቹና ቡናው በየቀኑ በእነዚህ የሥነ ማኅዳር ጥበቃ በሚደረግለት ቦታ በሚገኙት ጎጆዎች ውስጥ ለእንግዶች ይቀርባሉ። የተሰጣቸው የ 100,000 ብር ሥራ ማስጀመሪያ ድጋፍ አባላቱ የራሳቸውን ንግድ እንዲጀምሩና ያንን እንደገና ወደ ደንነት እንዲመለስ የተደረገውን ስፋቱ ወደ 200 ሄክታር የሚጠጋ አካባቢ የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያግዛቸዋል። ይህንን አካባቢ በአግባቡና በዘላቂነት ለመጠቀም እንዲችሉ የሚያግዟቸው መተዳደሪያ ደንቦች (ሕጋዊ ሰነዶችና መመሪያዎች) በ VoCDA እና IDH ድጋፍ በመዘጋጀት ላይ ናቸው።

Overview News

አዳዲስ የሕክምና መርጃ መሣሪያዎች ለሼር ሆስፒታል በስጦታ ተበረከተ፡፡

5 July 2022 Aswin Endeman

የኛ አጎራባች የሆኑት የአበባ እርሻ ድርጅቶች ኤኪው ሮዝስ፣ ብራም ሮዝስ፣ ሀርበርግ ሮዝስ እና ዝዋይ ሮዝስ የተለያዩ አዳዲስ የሕክምና መርጃ መሣሪያዎች በርዳታ ለሼር ሆስፒታል በቅርቡ በስጦታ ተሰጥተዋል። በዚህም መሠረት የሆስፒታላችን ሠራተኞች የልብ መመርመሪያ መሣሪያ (ኢሲጂ)፣ ሦስት የታካሚ ሰውነት መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች፣ እና የማዋለጃ አልጋ በእጃቸው ለማስገባት ችለዋል። ለሰጡን ድጋፍና በተለይም የድንገተኛ ሕሙማን ክፍላችንን ለማጠናከር ላበረከቱት አስተዋፅኦ እነዚህን ኩባንያዎች በዚህ አጋጣሚ ከፍ ያለ ምስጋናችንን ልናቀርብላቸዉ እንወዳለን።

ዝዋይ ውስጥ በሚገኙት 5 የአበባ እርሻዎች ዉስጥ የሚሠሩ በቁጥር 20000 የሚጠጉ ሠራተኞች ነጻ ሕክምና በሼር ሆስፒታል በኩል  ያገኛሉ ፡፡ እንዲሁም በየዓመቱ ቁጥራቸው ከ 100.000 የሚልቅ ፣ ከሠራተኞች፣ ከተማሪዎችና ከአካባቢው ማኅበረሰብ የተውጣጡ ታካሚዎች  በሆስፒታሉ ውስጥ የሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ።